ተፈጥሮ የራሷን ሚዛን የምትጠብቅበት የተለያዩ መንገዶች አሏት፡፡ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ከትልልቅ እንስሳት እስከ ትንንሽ ነፍሳት ያሉ ፍጥረታት በአዳኝና ታዳኝ፤ በበይና ተበይ ግንኙነት ተመስርቶ የሁለቱም ጎራ እንስሳትና ነፍሳት ቁጥር አንዴ ከፍ፤ አንዴ ደግሞ ዝቅ እያለ የበይና ተበይ የምግብ ሰንሰለት ከዚያም ከፍ ሲል የምግብ መረብን በመስራት ተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቃ እንድትቀጥል ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ህይወት ያላቸው ነገሮች እርስ በራሳቸውና ህይወት ከሌላቸው ነገሮች ጋር የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት የሌለበት መስተጋብር ብዝሃ-ህይወትን አቅፎ በመያዝ የስነ-ምህዳርን ጤነኝነት የሚያረጋግጥ ሂደት ነው፡፡ በሰፊው ስነ-ምህዳር ውስጥ የሚገኙ ሂደታቸው የተስተካከለ ጤናማ ስርዓተ-ምህዳሮች ተፈጥሮ ሚዛኗ እንዳይዛባ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ የእናት መሬት ታላቅ ስጦታዎች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቹን ለማሟላት በሚያደርጋቸው የየእለት ተግባራት እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት የሚደረግ ግብግቦች የተፈጥሮ ሚዛን በማዛባት በኢኮኖሚ እድገትና በጤናማ ስነ-ምህዳር መካከል የተፈከተ ጦርነት እየሆነ መጣ፡፡ የተፈጥሮ ሚዛንን ከሚያዛቡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ግብርና አንዱ ሲሆን በተለይም ደግሞ ለአፈር ለምነት መጨመሪያ እና ለተባይ መከላከያ የሚውሉ ሰው ሰራሽ የሆኑ ግብዓቶችን በብዛትና በአይነት የሚጠቀም የግብርና ስርዓት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ፤ ስርዓተ-ምህዳሩ በተጠበቀ አካባቢ የሚተገበር ግብርና ተፈጥሮአዊ የሆኑ የአፈር ለምነት መጠበቂያ እና የተባይ መከላከል ግልጋሎቶችን ያገኛል፡፡ በግብርና ስርዓት ውስጥ ለምርት መቀነስ ምክንያት በቀዳሚነት የሚጠቀሱትን ሰብል አውዳሚ ተባዮች ጤናማ የግብርና ስርዓተ-ምህዳርን በመገንባት የሚያስከትሉት